“S.Res.168” እና “H.Res.128”ን አስመልክቶ ከአማራ ማህበር በአሜሪካ እና ከአምባ የአማራ ባለሞያዎች ማህበር የተሰጠ የጋራ መግለጫ

AAA logo     APU logo

     መስከረም 09, 2010 ዓ.ም የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይዎች ንዑስ ኮሚቴ የኢትዮጵያ መንግስትን የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና መሰል ጉዳዮችን የሚዳስሰውን ረቂቅ ሕግ  “Senate Resolution 168” ያለምንም ተቃውሞ ወደ ቀጣዩ ሂዳት መርቶታል። ይህንን ረቂቅ ሰነድ ከዚህ ለማድረስ የአማራ ማህበር በአሜሪካ እና አምባ የአማራ ባለሞያዎች ማህበር የጋራ የቅስቀሳ(Advocacy) ኮሚቴ በመሰየም ስንደክምበት ቆይተናል። በዚህም የረቂቅ ሰነዱ ከዚህ ደረጃ መድረስ፣ ወደ ቀጣዩም ለሙሉ ምክር ቤት ምርጫ በሙሉ ድምጽ ማለፉ የማንኩራራበትን ደስታ ፈጥሮልናል። በዚህ ሂደት ውስጥ ለተሳተፋችሁ የድርጅቶቻችን አባላት እና ደጋፊዎች እንዲሁም በተለያየ መንገድ እና ሁኔታ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ላደረጋችሁ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች እና እንዲሁም አክትቪስቶች ላደረጋችሁት ከፍተኛ አስተዋጾ ምስጋናችን ይድረሳችሁ።.

     ይህንን በላይኛው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ለመጽደቅ በሂደት ላይ ያለውን ረቂቅ ሰነድ ጨምሮ  በታችኛው የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንዲሁ ለመጽደቅ በሂደት ላይ ያለው ረቂቅ ሰነድ “ House Resolution 128” የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ ያለጠያቂ የሚፈጽመውን በደል፣ ግድያ እና የሰብዓዊ መብት ረገጣ ያትታል። ረቂቅ ሰነዶቹ በሁለቱም ምክር ቤቶች የመጽደቅ እድል ካገኙ ፋሽስታዊው የወያኔ መንግስት፣ በስርዓቱ ውስጥ ተሳታፊ ሁነው ዜጎቻችንን የሚገድሉ እና የሚያሰቃዩ ባለስልጣናትን ጨምሮ በዚህ የተጠና የዘር ማጥፋት ወንጀል ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉ ለሚፈጽሙት በደልና ግፍ ተጠያቂ የሚሆኑበትን የሕግ አግባብ ይፈጥራል። በሁለቱም ረቂቅ ሰነዶች ተፈጻሚ እንዲሆን የተጠቆመው “ Global Magnitsky Human Rights Accountability Act” ፋሽስታዊውን የወያኔ መንግስት ባለስልጣናት በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ቢገኙ በሰሩት ወንጀል ለፍርድ እንዲቀርቡ ያስገድዳል። ይህም ዜጎችን እየገደሉ እና በማን አለብኝነት የሀገርን ሀብት እየዘረፉ በመላው ዓለም በድሎት የሚኖሩ ወንጀለኞችን ከያሉበት ለሰሩት በደል እና ወንጀል የሚመጥን ፍርዳቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል። ገንዘብ እና ሀብታቸው እንዳይንቀሳቀስ ያግዳል። ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ የቁም እስረኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህንንም የተረዳው ፋሽስታዊው የወያኔ መንግስት በሚሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር እያፈሰሰ ረቂቅ ሰነዶቹን ለማሰናከል እየሞከረ ይገኛል።

     ረቂቅ ሰነዶቹ በሁለቱም ምክር ቤቶች እንዲጸድቁ ከጸደቁም በኋላ ወንጀለኞችን በሕግ አግባብ ወደ ፍርድ ለማቅረብ የሁላችንንም የተባበረ ተሳትፎ ይጠይቃል። ዚህ በሰሜን አሜሪካ ለምትገኙ የፖለቲካ እና የስቪክ ድርጅቶች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የሀይማኖት ድርጅቶች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች እና እንዲሁም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ባለችበት ወቅት በዚህ ትልቅ ለውጥ በሚፈጥር የዜጎች ጩኽት ዘመቻ እንድትሳተፉ ጥሪያችንን እናቀርባላን።

    የአማራ ማህበር በአሜሪካ እና የአምባ የአማራ ባለሞያዎች ማህበር በዚህ ዘመቻ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ለሚፈልጉ ሁሉ የተሟላ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን ስንገልጽ ለምታደርጉት የነቃ ተሳትፎ ከወዲሁ የከበረ ምስጋና በማቅረብ ነው።

Is Amharic?
More To Read