አምባ/Amhara Professionals Union - መግቢያ

         የሰው ዘር መገኛ እና ከጥንታዊ ስልጣኔ ምንጭ መካከል አንዷ የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ በውስጧ የራሳቸው የተለያየ ባህልና ቋንቋ ያላቸው ህዝቦች ይገኙባታል። የአማራ ህዝብም በብዙነታቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ነው። የአማራው ህዝብ በክልል ሳይወሰን ከሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ጋር ተከባብሮና ተግባብቶ ለዘመናት በሰላምና በፍቅር የኖረ ህዝብ ነው። የአማራው ህዝብ እንደሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሁለገብ ብሄራዊ ጥቅም ፤ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መከበር ጉልህ አስተዋጽኦ ሲያበረክት የኖረና በሃገሪቱ ታሪክ ውስጥ በተደረጉ የነጻነት፡ የዲሞክራሲ እና የፍትህ ትግሎች ውስጥ ከፍተኛ መስዋእትነትም የከፈለ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደ ሃገር ባሳለፈቻቸው መልካምም ሆነ መጥፎ ክስተቶች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ድርሻ ያለው እንጂ በተለየ መልኩ ከባለፉት ስርአቶች ተጠቃሚ የሆነበት አጋጣሚ አልነበረም። በተለያዩ ጊዜያት ሀገሪቱን ያስተዳድሩ ከነበሩ መንግስታት የዲሞክራሲ፡ ፍትህ መጓደልና ልማት እጥረት በደል እንደማንኛውም የሃገሪቱ ዜጋ ሲደርሱበት ቆይቷል።

          ከታሪካዊ እውነታው በተቃራኒ ገና ከጥንስሱ አማራን በዋና ጠላትነት ፈርጆ የተነሳው የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ድርጅት (ህወሃት) ለከፋፍለህ ግዛው አላማው ይመቸው ዘንድ አማራ ባለፉት ስርአታት በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደሆነ በማስመሰል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ያካሂዳል። ይባስ ብሎም ህወሃት መራሹ መንግስት ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በታቀደና በተጠና መልኩ በአማራ ህዝብ ላይ የማሸማቀቅ፡ የጅምላ ግድያ፣ የማግለልና እንዲሁም ባህሉን ፣ ታሪኩን እና እሴቱን የማጥፋት ወንጀሎች እየፈጸመ ይገኛል። ይህንን በአማራ ህዝብ ላይ በህወሃት የተፈጸመዉን ግፍና የተጋረደውን የህልውና አደጋ ቀደም ብለው የተረዱት የአማራ ንቅናቄ ጀማሪ እና አቀጣጣይ በመባል የሚታወቁት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ አማራ ተደራጅቶ ለህልውናው መታገል እንዳለበት በማሰብ የመጀመሪያው የአማራ ድርጅት መመስረታቸው ይታወቃል። ሌሎችም የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች በተለያዬ ጊዜ የአማራ ህዝብ ራሱን ከጥቃት እንዲከላከልና ራሱን ጠብቆ ሃገሩን እንዲታደግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል። ነገር ግን ዘርን መሰረት አድርጎ መደራጀት በአማራ ህዝብ ዘንድ ያልተለመደ በመሆኑ የተነሳ የአማራውን ጥቅም የሚያስጠብቅ ጠንካራ የፖለቲካም ሆነ ሲቪክ ድርጅት መፍጠር አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬ በህወሃት መራሹ ፀረ ኢትዮጵያ መንግስት ከፈፋይ፡ጨለምተኛ እና ጥቅመኛ አገዛዝ የተነሳ የሃገራችን ኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ የአማራ ህዝብ ተፈጥሯዊ የመኖር መብት ከመቸውም ግዜ በላይ እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

        ስለዚህ በዚህ በታሪካችን እጅግ ፈታኝ በሆነ ወቅት በአንድነት ተሰባስቦ የአማራን ህዝብ ህልውና መታደግ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ተግባር እንደሆነ በማመን እኛ ከአማራ ህዝብ አብራክ የወጣን ባለሙያወች አምባን ህዳር 6 ቀን 2009 ዓ. ም መሰረትን። አምባ ትርፋማ ያልሆነ ሲቪክ ማህበር ሲሆን የተማረውን የሰው ሃይል እና በተለያየ መልኩ በአማራ ስም የተመሰረቱ ድርጅቶችን በማስተባበር እና በማንቀሳቀስ የአማራ ህዝብን ጥቅም እና እሴት ለማስጠበቅ ተግቶ ይሰራል። አምባ የአማራን ህዝብ መድሎአዊ ጥቃት ለማስቆምና የአማራን ህዝብ ለማጎልበት የምርምር እና ግንዛቤ መድረክ ሆኖ ይሰራል። አምባ በተጨማሪም ማህበራዊም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ያለባችውን ጥቃቅን ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው የበለጸገች፡አንድነቷ የተጠበቀ እና ድሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ እንዲሰሩ የመከባበር፡የመተባበር እና የመደማመጥ ባህልን ያስፋፋል።

           የአምባ መመስረት በምንም መልኩ በሀገራችን ሰፍኖ የሚገኘውን የጎጠኝነት እና የክፍፍል ፖለቲካን እውቅና የሚሰጥ ሳይሆን አጥብቆ የሚቃወም መሆኑ ግልፅ ሊሆን ይገባል። የአምባ መመስረት በዋናነት አማራው ህዝባችን ላይ የሚደርስበትን ጥቃት እንዲመክት ለማገልገልና ሀገራችን ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የቁልቁለት ጉዞ ለመታደግ ልንዘገይ አይገባም ከሚል አቋም የመነጨ ነው። በመሆኑም አምባ፤ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች ለሁላችንም የምትሆን ነጻ የበለጸገች እና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚችሉትን ሁሉ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪውን ያስተላልፋል።