የማህጸን በር ካንሰር (cervical cancer) መከላከያ ክትባት (HPV vaccine) በአማራ ሕዝብ ዘንድ

ጤና ለሰው ልጅ የተሰጠ ትልቁ ሃብት ነው። ሁሉ ነገር ተሟልቶ ጤንነት ከታወከ ተንቀሳቅሶ፡ ሰርቶና፡ ቤተሰብን መርቶ በደስታ መኖር አይቻልም። የጤንነት መታወክ የምክንያቱ ደረጃ ይለያይ እንጅ በየትም አገር የሚኖር የማንኛውም ማህበረሰብ እውነታ ነው። ስለሆነም አገሮች ሁሉ የዜጎቻቸውን ጤንነት ለመንከባከብ የጤና ተቋማትን አቋቁመውና ባለሙያዎችን አሰልጥነው የጤና ግልጋሎትን ይሰጣሉ። ከነዚህ የጤና ግልጋሎቶች አንዱ ክትባት ነው። በኢትዮጵያ የጤና እንክብካቤ አገልግሎት በጠቅላላው ብዙ የሚቀረው ቢሆንም በተለይ ‘አማራ ክልል’ በሚባለው ግን እጂጉን የባሰ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ህወሓት ዐማራን ለማዳከም የተከተለው ሁለገብ የጠላትነትና የጥቃት ዘመቻ  ነው።  የዐማራ ሕዝብ ለክፋት መሳሪያነት ይሆናሉ ብሎ ባልገመታቸው የጤና ዐገልግሎትም በኩል ጭምር ወያኔ ከፍተኛ በደል ስላደረሰበት በጤና ተቋማትና በባለሙያዎች የሚሰጡ እንደ ክትባት የመሳሰሉ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የጤና እንክብካቤዎችን በጥርጣሬ እንዲመለከትም የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሆኖም ግን ወገናችን መላው የዐማራ ሕዝብ ልብ እንዲል የምናሳስበው ክትባትን የመሳሰሉ አስፈላጊና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በጅምላ እንድንጠራጠር መደረጋችን ወያኔ እስካሁን ካደረሰብን የባሰ እልቂት ሊያስከትልብን የሚችል አደገኛ ሁኔታ ነው። ስለሆነም ክትባቶች በዓለምና በሌሎች የአገራችን አካባቢዎች የሚሰጡና የ’ክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን ቁጥጥርና ጥንቃቄ አድርጎ ሊያስገባው ስለሚችል ከመጠን ያለፈ ጥርጣሬ ወጥተን አስፈላጊ ክትባቶችን ልጆቻችን አንዲያገኙ እንድናደርግ አምባ የአማራ ባለሙያዎች ማህበር ይመክራል። 

Is Amharic?
More To Read